Empathy for Life Integrated Development Association

Sustainable development through empowerment!

የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ሚና

Share This Post

በ2001 አ.ም የወጣው የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ማህበራት ኤጀንሲ ህግ በተለይም ሀገር በቀል ለሆኑና በሰብአዊ መብቶች ዙሪያ ግንዛቤን ለመፍጠር ይሰሩ የነበሩ ድርጅቶችን ክፉኛ እንደጎዳ በሰፊው ይነገርለታል፡፡ ህጉ በ2012 እስኪሻሻል ድርስ፣ በርካታ መሀበራት፣ በጎ አድራጎት ድርጅቶችና የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋማት ፈርሰዋል፣ አልያም በእጅጉ ተዳከመዋል፡፡ በነዚህ አመታት በተደረጉ ምርጫዎች፣ የፖለቲካና መሀበራዊ ጉዳይ ክርክሮችና ውይይቶች፣ እንዲሁም የሴቶችንና የህጻናትን መብት ግንዛቤ መፍጠሪያ ሁነቶች በማህበራት ሳይወከሉ፣ በአንድ ወገን ድምጽ ብቻ ለህዝብ ሲቀርቡ አይተናል፡፡

በ2012 የወጣው አዲሱ ህግ በሀገሪቱ በተለይም ሰብአዊ መብቶች ላይ ትኩርት ለሚያደርጉ መሀበራትና በጎ አድራጎት ድርጅቶች የሚያመጣውን መልካም አጋጣሚና የጣለባቻውን ሀላፊነት ከማየታችን በፊት፣ የእነዚህ ተቋማት መኖር ለማህበረሰብ አጠቃላይ እድገት ያለውን ሚና እንመልከት፡፡

በጎ አድራጎት ድርጅቶችና መሀበራት፣ ከመገናኛ በዙሀን ባልተናናሰ መልኩ፣ የመንግስትን ስልጣንና ሀይል በመገዳደር፣ በመጠየቅና በመመርመር፣ የፖለቲካ ሀይሎች ሚዛናዊና ተጠየቂ እንዲሆኑ ያደርጋሉ፡፡ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች፣ የምርጫና የዲሞክራሲ ማጭበርበሮችን፣ የህግ ክፍተትናና ማሻሻያ መንገዶችን በመጠቆም፣ ጥቃት ለደረሰባቸው ጥብቅና በመቆምና ድምጻቸው እንዲሰማ በማገዝ፣ እንዲሁም ማህበረሰን በማስተማርና በማንቃት የሚጫወቱት ሚና እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ጥናቶች በተደጋጋሚ አሳይተዋል፡፡ እንዲሁም የዜጎች የመሰብሰብ.፣ የመናገር፣ የመጻፍና የመተቸት መገለጫዎች ስለመሆናቸውም ይነገራል፡፡ ለዚህም ነው፣ የዲሞክራሲ መርሆችን እተገብራለሁ ለሚል ማንኛውም አገርና መንግስት፣ መሀበራትና የበጎ አድራጎት ተቋማት በነጻነት በሚያሰራ የህግ ማእቀፍ ውስጥ መንቀሳቀስ የስኬት ቁልፍ ተደርጎ የሚወሰደው፡፡

 ዲሞክራሲን ለመተግበር፣ ሰብአዊ መብቶችን ለማክበርና ለማስከበር እንዲሁም ለህግ ተገዥ የሆነ ማህበረሰብን ለመፍጠር ህጎችና ፖሊሲዎችን ከማጽደቅና ለመተገበር ከመስራት ባለፈ፣ መርሆቹ የማህበረሰብ ባህልና አስተሳሰብ እንዲሆኑና በየእለት ህይወት ውስጥ እንዲተገበሩ መስራት ግድ ይላል፡፡ ይህንን ንቃተ ህሊና መፍጠር ታዲያ በዋነኛት በተለይም የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና መሀበራት ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ ተቋማቱ ከፖለቲካ ነጻ እንደመሆናቸው፣ የሚኖራቸው ተአማኒነትና ማህበረሰብ ጋር የመድረስ ጉልበት ለዚህ ውጤት መሰረት ነው፡፡ በተለይም መንግስት ችላ ሊላቸው የሚሞክራቸውን የመሀበረሰብ ችግሮች፣ ውጤታማ ያልሆኑ ፖሊሲዎችና አሰራሮች፣ ሙስና፣ በሴቶችና በህጻናት ላይ የሚደርስ ጥቃት፣ ጎጂ ባህላዊ ድርጊቶችና ሌሎች በአነስተኛ ቡድኖች ላይ የሚደርሱ የመብት ጥሰቶችን በማጥናት፣ በመመርመር በመረጃ የተደገፈ ሙግትን በማቅረብ፣ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን በመጠቆምና በማስተማር ውጤታማ መሆናቸውን የበርካታ ሀገራት ተሞክሮዎች አሳይተዋል፡፡

ለምሳሌ በርካታ ብሄርና ሀይማኖት ተኮር ግጭቶችን በምታስተናግደው ናይጄሪያ፣ ነገሮች ከቁጥጥር ውጭ እንዳይሆኑ መንግስት የሚደርገውን ጥረት በማገዝ፣ የተጋጩ ወገኖችን ለንግግር በመጋበዝና በማሸማገል ረገድ በጎ አድራጎት ድርጅቶች ቁልፍ ሚና ይጫወታሉ፡፡ ከእርስበርስ ጦርነት፣ ከዘር ማጥፋትና ከዘረኝነት ግጭቶች ተላቀው ሀገር ላማስቀጠል በቻሉት እንደ ሩዋንዳና ደቡብ አፍሪካ የመሳሰሉ ሀገራትም በተለይ ሀገር በቀል ተቋማት ያደረጉት አስተዋጽኦ ደጋግሞ ይጠቀሳል፡፡

በተለይም ሀገር በቀል ተቋማት፣ የማህበረሰቡ አካል እንደመሆናቸው መጠን፣ ስነልቦናን በመረዳት፣ ባህልና የአኗኗር ዘይቤን በማክበር፣ እንዲሁም በወገንተኝነትና በተቋርቋሪነት ስሜት ሊሰሩ መቻላቸው ሀገርን ለማሻገርና ማህበረብን ለማንቃት የሚኖራቸው ሚና እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡

የይህንን ድርሻ በጉልህ የሚያሳዩ ተሞክሮዎች በኛም ሀገር ታይተዋል፡፡ የኢትዮጵያ የህግ ባለሞያ ሴቶች ማህበርና የኢኮኖሚክስ ባለያዎች ማህበር እንደምሳሌ ብንጠቅስ፣ ማህበራቱ በየዘርፋቸው መንግስትን በመሞገትና ማህበረሰብን በማንቃት ያደረጉት አስተዋጽኦ በደማቁ ተጽፎላቸው እናገኘዋለን፡፡ ቀደም ባለው ጊዜ የጋዜጠኞች፣ የመምህራን፣ የጤና ባለሞያዎች መሀበራትም ያደርጉት የነበረው አስተወጽኦ በቀላሉ የሚታይ አልነበረም፡፡

በ2009 የጸደቀው ህግ ታዲያ እኒህን በማንሰራራት ላይ የነበሩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና መሀበራት እንቅስቃሴ በመግታት እድገታቸውን አቀጭጯል፡፡ ህጉ  የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ማህበራት ኤጀንሲን የቁጥጥር ስልጣንን ለመተገበር እስኪቸግር ድርስ በማስፋት፣ በተለይም የሰብአዊ መብትና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የሚሰሩ አገር በቀል ድርጅቶች የገቢና የወጪ ሂደት ላይ ከፍተኛ ማነቆ በማድረግ፣ እንዲሁም የአንዳንድ አንቀጾች ትርጓሜ ግልጽነት ማጣት ድርጅቶቹን ለችግር ስለመዳረጉ ጥናቶች አሳይተዋል፡፡  

ተከትሎ የወጣው የጸረ ሽብር ህግም የመናገርና የመሰብሰብ መብቶች ላይ ያስቀመጠው ከፍተኛ ገደብ፣ የማሀበራቱን አባላትና ሰራተኞች ስጋት እንዲያድርባቸውና ፖለቲካ ነክ ከሆኑ ነገሮች እንዲሸሹ ምክናያት ሆኖ ነበር፡፡

ህጉን በመተግበር ሂደት ላይ የበርካታ ተቋማት የባንክ አካውንት በመታገዱ ብዙዎቹ ስራ እንዲያቆሙና ጠንካራና ልምድ ያላቸውን ሰራተኞቻቸውን እንዲያጡ ምክናያት ሆኗል፡፡ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባወጣው መረጃ መሰረት ህጉ በወጣ በጥቂት አመታት ውስጥ ብቻ 17 ሀገርበቀል ጠንካራ ማህበራትና ድርጅቶች አላማቸውን በመቀየር በሰብአዊ መብቶችና በዲሞክራሲ ዙሪያ የነበሯቸውን ፕሮግራሞች ሙሉ በሙሉ ሰርዘዋል፡፡ በተለይም ጠንካራ እንቅስቃሴ በማድረግ ይታወቁ የነበሩት ኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ካውንስልና፣ የኢትዮጵያ የህግ ባለሞያ ሴቶች ማህበር በፕሮግራሞቻቸው ላይ ያደረጉት ለውጥ በምሳሌነት ይነሳል፡፡ በሂደትም በርካታ ድርጆትች ሙሙሉ በሙሉ ስራ ማቆማቸውና የቀረቱም በስም ብቻ መቆየታቸውን ሪፖርቶች ያሳያሉ፡፡

ህጉ አለም አቀፍ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች በሰብአዊ መብትና ዲሞክራሰ ጉዳዩች ላይ ጨርሶ እንዳይሰሩ በመከልከሉ፣ ተቋማቱ ቢሯቸውን እንዲዘጉ አልም አላማቸውን ወደአገልግሎትና እርዳታ ሰጪነት እንዲቀይሩ አድርጓል፡፡ ህጉና ተላላፈው ለተገኙም ቅጣቱ ከፍተኛ ገንዘብና ሰራተኞቹን ለእስር የሚዳርግ ነው፡፡

አዲሱ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና መሀበራት ህግ ታዲያ፣ እንዚህን ችግሮች በመዳሰስ መፍትሄ የሰጠ ነው፡፡ ህጉ ለማህበራትና በጎ አድራጎት ድርጅቶች ለስራ ምቹ የሆነና የሚያበረታታ ከባቢን ለመፍጠር አላማ እንዳለው ከመግቢያው ያትታል፡፡ በተለይም በዲሞክራሲ፣ በሰብአዊ መብት ጉዳዮች፣ በግጭት አፈታት፣ ፍትህን ለማስፈን የሚደረገውን ሂደት በማገዝ ዙሪያ የሚንቀሳቀሱ በጎ አድራጎት ድርጅቶች በሙሉ አቅማቸው መስራት እንዲችሉ ሁኔታዎችን ክፍት አድርጓል፡፡ ቀደም ብሎ በነበረው ህግ በሀገር በቀልና በውጭ ድርጅቶች መካከል ልዩነትን ፈጥሮ የነበረው የገንዘብ ምንጭ ጉዳይም፣ በወጥነት ሁሉም ህጋዊ ከሆነ ማንኛውም አካል ገንዘብ እንዲቀበሉና እንዲሰበሰቡ ስርአቱን ክፍት አድርጎታል፡፡

ይህ ለውጥ ይበል የሚሰኝ መሆኑን ደግሞ በተግባር ያየንበት የ2013 የኢትዮጵያ አጠቃላይ ምርጫ ነው፡፡ በርካታ ሀገር በቀል በጎ አድራጎት ድርጅቶችና መሀበራት በንቃት የተሳተፉበት ይህ ምርጫ፣ ብንጽጽር አበረታች እንደነበር ተመስክሮለታል፡፡ በተለይም የምርጫ ክርክሮችን በማስተባበርና በመምራት፣ ሴት ተመራጮችን የብቃት ስልጠናዎችን በመስጠትና፣ መራጮችን በማንቃትና በመቀስቀስ ተቋማቱ የደረጉት አስተዋጽኦ ይበል የሚያሰኝ ነበር፡፡ የ176 ሀገር በቀል ተቋማት ጥምረት ከ3000 በላይ የምርጫ ታዛቢዎችን በማሰማራት የምርጫውን ሂደት ሰላማዊ እንዲሆም፣ የመረጃ ፍሰቱ እንዲሻሻልና በተለይም ተፎካካሪ ፓርቲዎችን ቅሬታ በማንጸባረቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡

ህጉ በተተገበረ በአጭር ጊዜ ውስጥ፣ በርካታ መሀበራትና የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ከመመስረታቸውም በላይ፣ ያሉትም ወደቀድሞ ጥንካሬያቸው ለመመለስ የሚያደርጉት ጥረት ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡

የተፈጠረው መልካም አጋጣሚ በእርግጥም ለተቋማቱ የላቀ ሀላፊነትም ጭምር ነው፡፡ በተለይም በሀገራችን ለማጎልበት አዳጋች የሆነውን ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ የመፍታት ባህል በማጎለበት ረገድ  ከፍተኛ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ፡፡ አሁን ሀገራችን የደረሰበችበት ፖለቲካዊ ውጥንቅጥ፣ በአብዛኛው ከዲሞክራሲ ባህል አለመጎልበት ጋር ይያዛል፡፡ መነጋገር፣ መደራደር፣ የአብዛኛውን ድምጽ ማክበርና ሽንፈትን በጸጋ መቀበል፣ ሲያሸንፉም የአናሳውን ቡድን አስተያየት ማክበርና ባለመስማማት መስማማትን መቀበል በኢትዮጵያ ቀና ያላለ ባህል ነው፡፡ እንደማህበረሰብ ያለን የመቻቻልና የመከባበር ባህል፣ ለሽማግሌና ለሀይማኖት አባት የምንሰጠው ቦታ፣ ራስን ከሌሎች በላይ አድርጎ መቁጠርን የመጠየፍና ለአባዛኛው ጥቅምና ደህነነት ዋጋ የመክፈልና የመሳሳሉት በጎ ባህሎቻችን አድገውና ጎልበትው ፖለቲካዊ ማንነትን ሊገነቡ አልቻሉም፡፡ ለዚህም እጅግ ከባድ ዋጋ እየከፈልንበት እንገኛለን፡፡

እነዚህን ችግሮች ለመፍታ ሀገር በቀል መሀበራትና የበጎ አድራጎት ድርጅቶች በንቃት መሳተፍ ይኖርባቸዋል፡፡ በእርግጥም አሁን ያለንብት ችግር የሀገሩን መሬት በሀገሩ በሬ አይነት መፍትሄ የሚጠይቅ ነውና፣ የሞያ መሀበራትና በጎ አድረጎት ድርጅቶች የመፍተሄ ሀሳበች ላይ መረባረብ ይኖርባቸዋል፡፡ ከህግ ማእቀፉ ሳይወጡ ሀገርን ለመታደግ በሚደረገው ሩጫ ላይ በመሳተፍ በአግባቡ ሊጠቀሙበት ይገባል፡፡ የውይይት መድረኮችን በማስፋት፣ ሰላማዊ የግጭት አፈታት መንገዶች ላይ ግንዛቤን በመፍጠርና በማስተማር የሰላምን ጥቅም የሚረዳና የሀሳብ ልዩነትን የነገሮች ፍጻሜ አድርጎ የማይቆጥር ማህበረሰብን በማፍራት ረገድ የሚኖራቸው ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ በተለይም አሁን ባለንበት እሳት የማዳፈን አይነት ሩጫ ላይ፣ የመንግስት ፖሊሲዎችና አሰራሮች በረጅም ጊዜ ሀገር ላይ ስለሚያመጡት ውጤት የማጥናትና የመተንበይ፣ መንግስትም ከሩጫው ቆም ብሎ እንዲያስተውል በተለያዩ መንገዶች ግፊት የማድረግ ሀላፊነት ይኖርባቸዋል፡፡

ዲሞክራሲን ተቋማዊ ለማድረግ፣ ሰብአዊ መብቶችን ማክበርንና ለህግ መገዛትን ወደአኗኗር ዘይቤ ለመቀየር፣ ግጭቶችን በንግግር የመፍታትና የሀሳብ የበላይነት የማክበር ባህል ለማጎልበትከባለድረሻ አካላት ጋር በመተባበር ንቃተ ህሊናነ የመሳደግ ዘመቻ ለመጀመርም ጊዜው አሁን ነው፡፡

More To Explore

Uncategorized

የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ሚና

በ2001 አ.ም የወጣው የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ማህበራት ኤጀንሲ ህግ በተለይም ሀገር በቀል ለሆኑና በሰብአዊ መብቶች ዙሪያ ግንዛቤን ለመፍጠር ይሰሩ የነበሩ ድርጅቶችን ክፉኛ እንደጎዳ በሰፊው